
5 ግቦች በተቆጠረቡት በረፋድ ሶስት ሰዓት ጨዋታ ደሴ ከተማ ባለቀ ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ አሸንፏል። አምስቱም ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ወደሜዳ በመግባታቸው ኳስን ወደፊት ገፍተው ከመጫወት ይልቅ ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተሽሎ ለመገኘት ጥረት አድርገዋል። ቀድመው ቅያሪ ያደረጉት ደሴ ከተማዎች ከደብረብርሃን ከተማ የጨዋታ ብልጫ ቢወስዱም በ54ኛው ደቂቃ የደሴ ተጫዋቾች ኳስን እየገፉ ወደፊት ሄደው ሳይመልሱ ሲቀሩ ደብረብርሃኖች ያገኙትን እድል በሄኖክ አየለ አማካኝነት ወደግብነት ቀይረው መሪ መሆን ችለዋል። ነገር ግን በመሪነት የቆዩት ለአራት ደቂቃ ብቻ ነበር። በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የተገኙት ደሴ ከተማዎች በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በታየው በበሱፍቃድ ነጋሽ አማካኝነት የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል።
የአቻነት ግብ ከተቆጠረ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቄ ሲጫወቱ የተስተዋሉ ሲሆን ለ20 ደቂቃዎች ያህል አስቆጪ የሚባል የግብ ሙከራ አላስመለከቱም። ተቀይሮ የገቡት አቡሸ ደርቤ እና ሚካኤል ለማ በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ ወደተቃራኒ ቡድን በሚሄዱበት ግዜ በአቡሽ ደርቤ ላይ የደብረብርሃን ተከላካዮች ጥፋት ሰርተውበት ቅጣት ምት ተሰቷቸዋል። በ82ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ ተፈሠ ሠርካ ወድግብ ክልል አሻምቶ ዘሪሁን ዐቢይ ኳስና መረብ አገናኝቶ ደሴ ከተማ መሪ መሆን ችለዋል።
ደሴ ከተማ 2ለ1 እየመራ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ አልቆ ተጨማሪ በታየው 6 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን በ90+3 ደቂቃ ላይ ኢዮብ አስራት የደሴ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ሰህተት በመጠቀም ደብረብርሃን ከተማን አቻ አድርጓል።
ተጨማሪ ደቂቃ ሊያልቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ቀርተው እያለ በድጋሚ ደብረብርሃን ከተማዎች ጥፋት ሰርተው የቆመ ኳስ ለደሴ ከተማ ተስጥቷቸዋል።ያገኙትን ቅጣት ምት ኳስ ከመስመር አከባቢ ታፈሰ ሰርካ አሻምቶ ዘሪሁን ዐቢይ ጭፎ ወዴግብነት ቀይሮ ጨዋታው 3ለ2 በሆነ ውጤት በደሴ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
©Soccer Ethiopia