ሀዋሳ ላይ የፕሪምየር ሊጉን ክለብ ወላይታ ድቻን ከደሴ ከተማ ጋር ያገናኘው መርሀግብር ጥሩ የሆነ ፉክክርን አስመልክቶን በወላይታ ድቻ ድል አድራጊነት ተፈፅሟል። ተመጣጣኝ የሚመመስል የጨዋታ ቅርፅን ነገር ግን የወላይታ ድቻ የተደራጀ የማጥቃት ቅርፅን በተመለከትንበት ጨዋታ በቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ ድቻዎች መሐል ሜዳውን በአግባቡ ተቆጣጥሮ በመጫወት እና በተለይ ደግሞ የደሴ ተከላካዮች የሚሰሩትን የቅብብል ስህተት በመጠቀም ግቦች ለማስቆጠር በድግግሞሽ ጫና ሲፈጥር ተመልክተናል። 21ኛው ደቂቃ ላይ የደሴ ተጫዋቾች ኳስን ሲቀባበሉ የፈጠሩትን ስህተት ቢኒያም ፍቅሬ በፍጥነት ነጥቆ ከፀጋዬ ብርሀኑ ጋር አንድ ሁለት ቅብብልን ካደረገ በኋላ ፀጋዬ በመጨረሻም ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ተጠቅሞ ቢኒያም ከመረብ አሳርፎ የጦና ንቦቹን መሪ አድርጓል። ደሴዎች ኳስን በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባቱ ረገድ ቢሳካላቸውም በአንድ ሁለት ቅብብል ወቅት በሚፈጥሩት ስህተት መጋለጣቸው ያልቀረለት ቡድኑ ተጨማሪ ግብን ለማስተናገድ ተገደዋል። ጨዋታው ሊገባደድ 45+1 ላይ አብነት ደምሴ ለቢኒያም የሰጠውን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ በግራ የግብ ክልል ገፋ ካደረገ በኋላ ሁለተኛ ጎል በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል በ2ለ0 ውጤት አምርቷል።

ከዕረፍት የተመለሰው የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር ቀጥሎ በንፅፅር የወላይታ ድቻ የበላይት የታየበት ነበር። መሐል ሜዳውን አሁንም ተቆጣጥረው ወደ መስመር በመለጠጥ ሲጫወት የነበረው ቡድኑ ከፍ ባለ ተገሳሽነት ሦስተኛውን ግብ አግኝተዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ከራስ ሜዳ ኳስን ለማስጀመር ሲሉ ስህተቶቻቸው በጉልህ የሚታይባቸው ደሴዎች በተጠቀሰው ደቂቃ አብነት ደምሴ ነጥቆ ከብዙአየው ጋር ካደረገው ቅብብል በኋላ አበባየው አጂሶ ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ፀጋዬ በቶሎ ነፃ ቦታ ለነበረው ዮናታን ኤልያስ አቀብሎት አማካዩ ሦስተኛዋን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው ወደ 3ለ0 ተሸጋግሯል። ሦስት ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ በይበልጥ የገቡት ደሴ ከተማዎች ከሽንፈት ያላዳናቸውን ኳስ 63ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥርዋል። በረጅሙ ከግራ በኩል የደረሰውን ኳስ በድቻ ተከላካዮች መሐል ሾልኮ በመውጣት ተቀይሮ የገባው ካሳሁን አስቆጥሮ ጨዋታው በወላይታ ድቻ የ3ለ1 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።

ምንጭ: ሶከር ኢትዮጵያ